languageIcon
search
search
brightness_1 አንድ የሚያነጥስ ሰው ካስነጠሰው በኋላ “አልሐምዱሊልላህ” ማለቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው

አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንዳችሁ ካነጠሰ ‹አልሐምዱሊልላህ› ይበል፡፡ ወንድሙ ወይም ባልንጀራው፣ ‹የርሐሙከልላህ፡፡ /አላህ ይማርህ፡፡/ ይበለው፡፡ አላህ ይማርህ ካለው፣ ያነጠሰው ሰው ‹የህዲይኩሙ-ልላሁ ወዩስሊሑ ባለኩም፡፡ /አላህ ቀጥተኛውን መንገድ ይምራችሁ፡፡ ሁኔታችሁንም ያስተካክልላችሁ፡፡/” ይበል፡፡” ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (6224) ላይ ዘግበውታል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ካነጠሰ በኋላ የሚለውን ዚክር መለያየቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ ስለዚህም አንዳንድ ጊዜ፣ ‹‹አልሐምዱ-ሊልላህ ዐላ ኩልሊ ሓል፡፡/ በሁሉም ሁኔታ ላይ ለአላህ ምስጋና ይገባው፡፡/ ይላል፡፡ በአቢ ዳዉድ ዘገባ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንዳችሁ ካነጠሰ አልሐምዱሊልላህ ዐላ ኩልሊ ሓል ይበል” ብለዋል፡፡ አቢ ዳዉድ ሐዲሡን በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (5031) ላይ የዘገቡት ሲሆን ኢብን አል-ቀይዪም -አላህ ይዘንላቸው- ዛዱ-ል-ሚዓድ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቅጽ፡ 2 ገጽ ፡ 436 ላይ የሐዲሡ የዘገባ ሰነድ ትክክል ነው ብለዋል፡፡

የሚሰማው ሰው፣ “የየርሐሙከ-ልላህ፡፡ /አላህ ይማርህ፡፡/” ይለዋል፡፡ ያነጠሰው ሰውም እንዲህ ላለው ሰው፣ “የህዲይኩሙ-ልላሁ ወዩስሊሑ ባለኩም፡፡/አላህ ቀጥተኛውን መንገድ ይምራችሁ፡፡ ሁኔታችሁንም ያስተካክልላችሁ፡፡/” ማለቱ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡  ይህን ሁሉ ከዚህ በላይ ያሳለፍነው የአቡ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ሐዲሥ አመልክቷል፡፡

 

brightness_1 አንድ ሰው አነጥሶት አላህን ካላመሰገነ አላህ ይማርህ አለማለት ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡

ያስነጠሰው ሰው አላህን ካልመሰገነ አላህ ይማርህ ማለት ነቢያዊ ፈለግ አይደለም፡፡ በአንጻሩ አላህ ይማርህ አለማለቱ ነው ነቢያዊ ፈለጉ፡፡ አነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት፣ ‹‹ሁለት ሰዎች ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- አነጠሱ፡፡ አንደኛውን አላህ ይማርህ ሲሉት ሌላኛውን አላሉትም፡፡ አንደኛው ሰውዬ፣ ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህን ሰው አላህ ይማርህ አሉት፤ እኔን ግን አላህ ይማርህ አላሉኝም፡፡› አላቸው፡፡ እሳቸውም፣ “ይኸኛው አላህን አመሰገነ፣ አንተ ግን አላህን አላመሰገንክም፡፡” አሉ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን  ቡኻረ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (6225) ላይ ዘግበውታል፡፡ ይህ እንዲህ ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- የፈጸሙት ተግባር ነው፡፡ የተናገሩትን ቃል ደግሞ ሙስሊም ከአቢ ሙሳ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- የዘገቡት ሐዲሥ ነው፡፡ በዚህ ሐዲሥ ላይ አቢ ሙሳ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹ የአላህ መልከእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ከእናንተ መካከል አንዳችሁ ካነጠሰና አላህን ካመሰገነ አላህ ይማርህ በሉት፡፡ አላህን ካላመሰገነ አላህ ይማርህ አትበሉት፡፡” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2992) ላይ ዘግበውታል፡፡

ነገር ግን ልክ አባት ልጁን ወይም መምህር ተማሪውን  እንደሚያስተምረው ወ.ዘ.ተ ዓይነት የማያውቀውን ሰው ይህን ነቢያዊ ፈለግ ለማስተማር ከሆነ ‹‹አልሐምዱሊልላህ፡፡›› በል ይለዋል፡፡

እንደዚሁ ሰውየው ጉንፋን የያዘው ከሆነ ከሶስተኛው ማስነጠስ በኋላ አላህ ይማርህ አይባልም፡፡ ሶስት ጊዘ ካስነጠሰ ግን አላህ ይማርህ ይባላል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አይባልም፡፡

ለዚህ ማስረጃው፡- አቡ ዳዉድ ሱነን በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ከአቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ወንድምህን ሶሰት ጊዜ አላህ ይማርህ በለው፡፡ ከዚያ በላይ ከጨመረ እሱ ጉንፋን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ ሐዲሡን አቡ ዳዉድ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (5034) ላይ የዘገቡት ሲሆን አል-አልባኒይ ሐዲሡን መውቁፍና መርፉዕ ነው ብለዋል፡፡ ሰሒሑ አቡ ዳዉድ ቅጽ ፡ 4 ገጽ ፡ 308፡፡ 

 ይህን ሐዲሥ ሙስሊም በትክክለኛ የሐዲሥ ዘገባቸው ከሰለመተ ኢብን አል-አክወዕ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደዘገቡት፣ ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ዘንድ አንድ ሰው ሲያነጥስ፣ “አላህ ይማርህ፡፡” አሉት፡፡ እንደገና አነጠሰ የአላህ መልእከተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “ሰውየው ጉንፋን የያዘው ነው፡፡” ሲሏቸው ሰምተዋል የሚለው ሐዲሥ ይደግፈዋል፡፡ ሐዲሡን ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2993) ላይ ዘግበውታል፡፡

ከዚህ በላይ ከሰፈረው አንድ ያስነጠሰው ሰው በሁለት ሁኔታዎች አላህ ይማርህ አይባልም፡፡ እነርሱም፡-

1. -በእጅጉ የላቀውን- አላህን  ካላመሰገነ፣

2. ከሶስት በላይ ካስነጠሰ፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰው ጉንፋን ይዞታልና ነው፡፡