languageIcon
search
search
brightness_1 በምግቡ መጀመሪያ ላይ የአላህን ስም ማውሳት

ዑመር ኢብን አቢ ሰለመህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣   ‹‹በአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ቤት ውስጥ ልጅ ነበርኩኝ፡፡ እጄ መመገቢያ ትሪውን ይነካካ ነበር፡፡ እንዲህ አሉኝ፣ “አንተ ልጅ ሆይ! የአላህን ስም አውሳ፡፡ በቀኝህም ተመገብ፡፡ ከፊት ለፊትህም ተመገብ፡፡” ከዚያች ጊዜ አንስቶ አመጋገቤ እንደዚያ ከመሆን አልተወገድም፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን  ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (5376)፣ ሙስሊም ደግሞ በቁጥር (2022) ላይ ዘግበውታል፡፡

ለአንድ ሙስሊም የተሻለው የአላህን ስም ማውሳትን አለመተዉ ነው፡፡ የአላህን ስም ማውሳቱን ከረሳና ካስታወሰ፣ ‹ቢስሚልላህ አውወለሁ ወኣኺረሁ፡፡ በመጀመሪያውም በመጨረሻው ላይ በአላህ ስም፡፡/› ማለቱ ነቢያዊ ፈለግ  ነው፡፡

ዓኢሻህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- “አንዳችሁ ሲመገብ የአላህን ስም ያውሳ፡፡ የአላህን ስም በመጀመሪያው ላይ ማውሳትን ከረሳ ቢስሚልላህ አውወለሁ ወኣኺረሁ፡፡ በመጀመሪያውም በመጨረሻው ላይ በአላህ ስም፡፡/ ይበል፡፡” ማለታቸውን የዘገቡበት ሐዲሥ ነው፡፡  ሐዲሡን አቢ ዳዉድ በቁጥር (3767)፣ አት-ቲርሚዚይ በቁጥር (1858) የዘገቡት ሲሆን አል-አልባኒይ ትክክለኛነቱን አረጋግጠዋል፡፡ ሰሒሑ-ልጃሚዕ ቅጽ ፡ 1 ገጽ፡ 282፡፡

ሐዲሡ አንድ ሲመገብ ከሸይጣን ጋር እንዳይመሳሰል በቀኝ እጁ መመገብ እንዳለበት አረጋግጧል፡፡ አንድ ሙስሊም ሲመገብ የአላህ ስምን ካላወሳ በምግቡ ላይ ሸይጣን ይጋራዋል፡፡ በግራ እጁ ከተመገበ ወይም ከጠጣ በዚህ ድርጊቱ ሸይጣንን ተመሳስሏል፡፡ ምክንያቱም ሸይጣን የሚመገበውም የሚጠጣውም በግራው ስለሆነ ነው፡፡

ሸይጣን ወደአንድ ቤት ውስጥ የመግባት፣ በውስጡም የማደርና ከቤቱ ቤተሰቦች ጋር ምግብን የመጋራት ከፍተኛ ጉጉት አለው፡፡ ጃቢር ኢብን ዐብዱላህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንድ ሰው ወደቤቱ ሲገባ በምግባቱና በምግቡ ላይ የአላህን ስም ካወሳ ሸይጣን፡- ማደሪያና እራት የላችሁም ይላል፡፡ ሰውዬው ሲገባ በመግባቱ ላይ የአላህን ስም ካላወሳ ሸይጣን፡- ማደሪያ አገኛችሁ፡፡ በምግቡ ላይ የአላህን ስም ካላወሳ ሸይጣን፡- ማደሪያና እራት አገኛችሁ፡፡ ይላል፡፡” ሲሉ መስማታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሐዲሡን ሙስሊም በሐዲሥ ቁጥር (2018) ላይ ዘግበውታል፡፡

brightness_1 የወደቀችውን ቁራሽ ማንሳትና በላዩዋ ላይ ያለውን ጎጂ ነገር ማስወገድና መመገብ

ጃቢር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “በርግጥ ሸይጣን አንዳችሁን በሁሉም ሁኔታው ላይ ይመጣበታል፡፡ ምግቡ ላይም ሳይቀር ይመጣል፡፡ ከአንዳችሁ አንዳች ቁራሽ ብትወድቅ በላዩዋ ላይ ያለውን ጎጂ ነገር ያስወግድና ከዚያ ይብላት፡፡ ለሸይጣን ፈጽሞ አይተዋት፡፡ ከጨረሰ ጣቶቹን ይላስ፡፡ የምግቡ በረካት በየትኛው የምግቡ ክፍል ላይ እንዳለ አያውቅምና፡፡” ሲሉ     ሰምቻለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሙስሊም  በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2033) ላይ ዘግበውታል፡፡

ይህን ሐዲሥ የሚያስተውል በርግጥ ሸይጣን አንድን ሰው በሁሉም ነገሮቹ ላይ ለመጋራት፣ በረከትን ከእሱ ላይ ለማስወገድ፣ በርካታ ሁኔታዎቹን ሊያበላሽበት ጉጉት እንዳለው ይረዳል፡፡ ሸይጣን ከአንድ ሰው ጋር ለመቆራኘት ፍላጎት እንዳለው ከሚያረጋግጡልን መካከል፣ “በርግጥ ሸይጣን አንዳችሁን በሁሉም ሁኔታው ላይ ይመጣበታል፡፡” የሚለው የነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ሐዲሥ ነው፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች መካከል የተወሰኑትን ግልጽ የሚያደርጉ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ከዚህ በፊት ያሳለፍነው በምግብና በማደሪያ ላይ የሰፈሩት ሐዲሦች አብነት ይጠቀሳሉ፡

brightness_1 የመመገቢያ ትሪውን ማጽዳት

የመመገቢያ ትሪውን ማጽዳት ማለት በሚበላበት አካባቢ ያለውን ሥፍራ ንጹሕ አድርጎ ማጽዳት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሰውዬው ሩዝ የሚበላ ከነበር ነቢያዊ ፈለጉ ከፊት ለፊቱ አንዳች ነገር አለመተዉ፣ የተቀረውን ማበሱና መብላቱ ነው፡፡ ምናልባትም የምግቡ በረከት ያለው በዚህ በቀረውና በማይተወው ላይ ይሆናል፡፡

ለዚህም ማስረጃው፡- አነስ -አላህነ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ትሪውን እንድናጸዳ አዘዙን፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ሙስሊም በሐዲሥ ቁጥር (2034) ላይ ዘግበውታል፡፡ በሌላ የሙስሊም ዘገባ አቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንዳችሁ ትሪውን ያጽዳ፡፡” ብለዋል፡፡ሙስሊም በሐዲሥ ቁጥር (2035) ላይ ዘግበውታል፡፡

ሸይኻችን ኢብን ዑሠይሚን -አላህ ይዘንላቸው-፣ ‹‹ትርጉሙ ምግብ የቀረበትን ሥፍራ እየተከታተልክ በጣቶችህ በማስወገድ ጣትህን መላስ ነው፡፡ የሚሳዝነው የዲን ትምህርት ተማሪዎችንም ቢሆኑ ይህ እንደዚሁ ነው፡፡›› ሸርሑ ሪያዱ-ስሳሊሒን ቅጽ ፡ 1 ገጽ ፡ 892፡፡

brightness_1 ከእቃው ውጭ ሶስት ጊዜ መተንፈስ

በእቃ ውስጥ ላይ ያለን ውሃ በሶሰት ጊዜ መጠጣትና በእያንዳንዱ መጠጣት በኋላ መተንፈስ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡

ለዚህ ማሰረጃው፡- አነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- በመጠጥ ላይ ሶስት ጊዜ ይተነፍሱና፣ “በርግጥ እሱ አርኪ፣ ፈዋሽና እጅግ ጣፋጭ የሆነ ነው፡፡” ይሉ ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ አነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዲሁ፣ ‹‹በመጠጥ ላይ ሶስት ጊዜ እተነፍሳለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሀዲሥ ዘገባ ቁጥር (5631)፣ ሙስሊም በቁጥር (2028) ላይ ዘግበውታል፡፡

መተንፈስ ማለት ሲጠጡ ከእቃው ውጭ ይተነፍሱ ነበር ማለት ነው፡፡ በውሃው ላይ መተንፈስ የተጠላ ተግባር ነው፡፡ አቢ ቀታደህ -አላህ መልካም ሥረዎቻቸውን ይውደድላቸው- ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሐዲሥ ላይ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “አንዳቸሁ ከጠጣ በእቃው ውስጥ አይተንፍስ፡፡” ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (5630)፣ ሙስሊም በቁጥር (267) ላይ ዘግበውታል፡፡

 

brightness_1 አንድ ሰው ምግቡ ደስ ካለው ማወደስ

አንድ ሰው የሚመገበው ምግብ ደስ ካለው በእርግጥ በውሰጡ ባለው እንደሚያወድሰው ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ ከነቢያዊ ፈለጎች መካከል ነው፡፡

ለዚህ ማስረጃው፡- ጃቢር ኢብን ዐብዲላህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ነበዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ቤተሰባቸውን ዳቦ ማባያ ነገር ጠየቁ፡፡ እነሱም፡- ‹ከኮምጣጤ በስተቀር ምንም ነገር የለንም› አሏቸው፡፡ እንዲመጣ አደረጉ፡፡ ዳቦውን ይበሉበት ጀመሩና፣ “ግሩም ማባያ ኮምጣጤ ነው፡፡ ግሩም ማባያ ኮምጣጤ ነው፡፡” አሉ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ሙስሊም በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (2025) ላይ    ዘግበውታል፡፡ እነሱ ዘመን የነበረው ኮምጣጤ አሁን በኛ ዘመን እንዳለው ኮምጣጤ አይደለም፡፡ አይቆመጥጥም፡፡ ለማባያነት ያገለግላል፡፡ 

ሸይኻችን ኢብን ዑሠይሚን -አላህ ይዘንላቸው-፣ ‹‹ይህ እንዲሁ ከነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- አስተምህሮዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በርግጥ እሳቸው አንዳች ምግብ ደስ ካላቸው ያወድሱት ነበር፡፡ ለምሳሌ ዳቦን ስታመሰግን ፡- እነ እከሌ የጋገሩት ዳቦ ምነኛ ግሩም ዳቦ ነው! ወይም የመሳሰለውን ትላለህ፡፡ ይህ እንዲሁ ከአላህ መልእክተኛ-የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ፈለጎች መካከል ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ ሸርሑ ሪያዱ-ስሳሊሒን ቅጽ ፡ 2 ገጽ ፡ 1057፡፡

ነባራዊ ሁኔታችንን ላየ በርካታ የነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ፈለጎችን እንደምንቃረን ይታዘባል፡፡ ሰዎች ነቢያዊ ፈለገን መተው ብቻ አይደለም ጭራሽ ተቃርነውታልም፡፡ ከነዚህ መካከል ምግብ ማነወር አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ያንቋሽሻሉ፡፡ ይህ የነቢዩን -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- አስተምህሮዎችን መቃረን ነው፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም ከአቢ ሁረይራህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንደዘገቡት፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ፈጽሞ አንድም ጊዜ ምግብን አነውረው አያውቁም፡፡ ከወደዱት ይመገቡታል፡፡ ያለዚያ    ይተዉታል፡፡›› ብለዋል፡፡ ሐዲሡን ቡኻሪ በሐዲሥ ዘገባ ቁጥር (3563)፣ ሙስሊም በቁጥር (2064) ላይ ዘግበውታል፡፡

brightness_1 የሚጠጣ ሰው ከግራው ይልቅ በቀኙ በኩል ያለውን ሰው ማጠጣቱ የተወደደ ተግባር ስለመሆኑ

ይህ ማለት አንድ ሰው አንዳች ነገር ከጠጣ በኋላ የሚጠጣውን ነገር በቀኝ በኩል ላለው ሰው ማስተላለፉ  ነቢያዊ ፈለግ ነው ማለት ነው፡፡

ለዚህ ማስረጃው፡- አነስ ኢብን ማሊክ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ወደቤታችን መጡ፡፡ የሚጠጣ ነገር እንዲመጣላቸው ጠየቁ፡፡ ፍየላችንን አለብንላቸው፡፡ ከዚያ ከዚህ ምንጬ ውሃ ሰጠኋቸው፡፡ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ አቡ በክር በግራቸው፣ ዑመር በፊት ለፈታቸው እንዲሁም አንድ ገጠሬ ሰው በቀኛቸው በኩል    ነበሩ፡፡ የአላህ መልእክተኛ የሚጠጡትን ጠጥተው ከጨረሱ በኋላ ዑመር እያመላከቷቸው፣ ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህ አቡ በክር ናቸው፡፡› አሉ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ለገጠሬው ሰጡት፡፡ አቡ በክርንና ዑመርን ተዉ፡፡ ከዚያም የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “የቀኝ ጓዶች፣ የቀን ጓዶች፣ የቀኝ ጓዶች፡፡” አሉ፡፡ አነስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣‹‹እሷ ሱንና ነች፡፡ እሷ ሱንና ነች፡፡ እሷ ሱንና ነች፡፡›› አሉ፡፡ ቡኻሪ በቁጥር (2571)፣ ሙስሊም በቁጥር (2029) ላይ ዘግበውታል፡፡  

brightness_1 ሰዎችን የሚያጠጣ ሰው መጨረሻ ላይ የሚጠጣ ስለመሆኑ

ሰዎችን የሚያጠጣ ሰው መጨረሻ ላይ መጠጣቱ ነቢያዊ ፈከግ ነው፡፡

ለዚህ ማስረጃው፡- ረዘም ባለው የአቢ ቀታዳህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- ሐዲሥ ውስጥ፣ ‹‹…የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ከአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- እና ከእኔ ውጭ ማንም ሳይቀር የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-እየቀዱ እኔ አጠጣ ነበር፡፡ ከዚያ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ቀዱና፣ “ጠጣ” አሉኝ፡፡ እኔም፣ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እርስዎ እሰኪጠጡ ድረስ አልጠጣም፡፡ አልኳቸው፡፡ እሳቸውም፣ “እኔ ሰዎችን አጠጪና በመጨረሻቸው ጠጪ ነኝ፡፡” አሉ፡፡ እኔም ጠጣሁ፡፡ የአላህ መልእክተኛም ጠጡ፡፡…››  ብለዋል፡፡ ሙስሊም በቁጥር (681) ላይ ዘግበውታል፡፡

ፋይዳ፡- አንድ ሰው ወተት የጠጣ ከሆነ ወተት በመጠጣቱ በውሃ መጉመጥመጡ ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡ ይህም አፉ ውስጥ ያለው የወተቱ ቅባት እንዲለቅ ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃው፡- ኢብን ዐብባስ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው-፣ ‹‹ነቢዩ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን- ወተት ጠጡ፡፡ ውሃ እንዲመጣላቸው አዘዙ፡፡ ከዚያም ተጉመጠመጡና፣ “በርግጥ እሱ ቅባት ነው፡፡” ቡኻሪ በቁጥር (211)፣ ሙስሊም በቁጥር (358) ላይ ዘግበውታል፡፡

 

brightness_1 በሚመሽበት ወቅት እቃዎችን መክደንና የአላህ ስምን ማውሳት

ሲመሽ ክፍት የሆኑ እቃዎችን መክደን፣ ማጠጫዎችን ማጋደም ግጣም ካለቸውም መዝጋትና በዚህ ጊዜም የአላህን ስም ማውሳት ነቢያዊ ፈለግ ነው፡፡

ለዚህ ማሰረጃው፡- ጃቢር ኢብን ዐብዲላህ -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- እንዳስተላለፉት፣‹‹ የአላህ መልእክተኛ -የአላህ እዝነትና ሰላምታ በእሳቸው ላይ ይሁን-፣ “እቃን ክደኑ፡፡ ማጠጫዎችንም ግጠሙ፡፡ በአመት ውስጥ በሽታ የሚወርድበት ሌሊት አለ፡፡ ክዳን በሌለበት እቃ ወይም ግጣም በሌለበት ማጠጫ በኩል ከዚያ በሽታ ላይ  አንዳች በሽታ ሳያወርደበት አያልፍም፡፡” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡ ሙስሊም በቁጥር (2014) ላይ የዘገቡት ሲሆን ቡኻሪ ከጃቢር -አላህ መልካም ሥራዎቻቸውን ይውደድላቸው- በዘገቡት ሐዲሥ ላይ እንዲሁ፣ “አኮሌያችሁንም ግጠሙ፡፡ የአላህን ስምንም አውሱ፡፡ እቃዎቻችሁንም ሸፍኑ፡፡ የአላህንም ስም አውሱ፡፡ አንዳች ነገር በእሷ ላይ ብታጋድሙም፡፡” ብለዋል፡፡ ቡኻሪ በቁጥር (5623) ላይ ዘግበውታል፡፡